Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዩ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአቮካዶ ልማት ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል – አቶ አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቀጣይ በልዩ ትኩረት ከሚሰራባቸው አንዱ የአቮካዶ ልማት ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ።
ለቀጣይ 15 ዓመታት የሚቆይ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ማብሰሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ብሔራዊ የልማት ፕሮግራሙ ዋና ትኩረት የአቮካዶ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ሲሆን 38 ነጥብ 57 ቢሊየን ብር በጀት ተመድቦለታል።
‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአረንጓዴ አሻራ በቀጣይ እንደየአካባቢዎቹ ተስማሚ ሁኔታ በተለይም ለምግብነት በሚውሉ ዕጽዋቶች ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ መስጠታቸውን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራሙ በዚሁ አቅጣጫ መሰረት መጀመሩን ጠቅሰው ፥ መርሐ ግብሩ እንዲሳካ በእውቀት፣ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመናበብና ሰፊ ክትትል በማድረግ መተግበር አለበት ብለዋል።
ፕሮግራሙ በአቮካዶ የለማውን 100 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ 191 ሺህ ሄክታር ማሳደግ የሚያስችል ሲሆን፥ ምርታማነትን በማሳደግ በሄክታር 13 ቶን የነበረውን ምርት ወደ 24 ቶን ከፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ብሔራዊ መርሐ ግብሩ ዓመታዊ የአቮካዶ የምርት መጠንን ከ400 ሺህ ቶን ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
‎የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስና ጥራትን ማስጠበቅ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ግብይትን ማሻሻል፣ በአቮካዶ ምርት እሴት ሰንሰለት የምርምር፣ ስልጠናና ኤክስቴንሽን ሥርዓት አቅምን ማሳደግ ላይ በማተኮር ይሰራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በፕሮግራሙ 3 ሚሊየን ባለ አነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን ፥ ሙሉ በሙሉ ሲተገበር ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የአቮካዶ ላኪ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ያደርጋታል።
አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ‎በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የማብሰሪያ መርሐ ግብሩ አካል የሆነ የአቮካዶ ምርት የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.