የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ አካላት ከግማሽ ርቀት በላይ ተጉዘን እናስተናግዳለን – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም አማራጭን ከማስፋት ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተሰጡ አቅጣጫዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ አካላት ምንጊዜም ከግማሽ ርቀት በላይ ተጉዘን እናስተናግዳለን ብለዋል፡፡
ከሰላም አኳያ በሀገራችን ውስን አካባቢዎች የሰላም ችግር እንደነበር ጠቅሰው÷ አሁን ላይ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ሰላምና ጸጥታ የተረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰላምና የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ለመቀየር ሰፊ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ውጤት መገኘቱን ጠቁመው ÷ በቀጣይ በቀሪ ቦታዎች ከሕዝብ ጋር በመሆን ሰላምና ጸጥታን እንዲሁም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡
ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ያለው አካል ጥያቄውን የተፈጠረውን ምቹ ምሕዳር በመጠቀም በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማቅረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ለሰላም አማራጭ ሁሌም በራችን ክፍት ነው፤ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ አካላትን ምንጊዜም ከግማሽ ርቀት በላይ ተጉዘን የምናስተናግድ ይሆናል ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
የሰላም አማራጭን ከማስፋት ጎን ለጎን ከሕዝብ ጋር በመሆን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ሥራ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ