Fana: At a Speed of Life!

በብልሹ አሰራርና ሌብነት የሚሳተፉ አመራሮች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሃላፊነቱን በሚገባ በማይወጣ እና ሕዝቡን በታማኝነት የማያገለግል አመራር ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተሰጡ አቅጣጫዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ባለፉት ሶስት ወራት የብልጽግና ፓርቲን ተቋማዊ አቅም የሚያጠናክሩ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡
ይህ የአቅምና የክህሎት መጎልበትም እንደ መሪ ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡
በተለይም አመራሩን እና አባሉን ለተልዕኮ ለማዘጋጀት የተከናወኑ ሥራዎች ተግባቦትንና ክህሎትን ከመፍጠር አንጻር ውጤታማ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡
የፓርቲውን አመራርና አባላት የመገምገምና የመመዘን ሥራ መከናወኑን ጠቁመው ÷ በዚህም እውቅና እና ምስጋና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡
በአንጻሩ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ 8 ሺህ 613 አመራሮች ለይ የዲሲፕሊን ርምጃ ተወስዷል ያሉት አቶ አደም ፋራህ ÷ ርምጃው ከሃላፊነት ማንሳት፣ ከደረጃ ዝቅ ማለት እና ሽግሽግን ያከተተ ነው ብለዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል እንዲያረጋገጥ አመራሩና አባላት ሕግና ሥርዓትን እንዲሁም ደንብና መመሪያን አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይ የተሰጠውን ሃላፊነት በሚገባ በማይወጣ፣ ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት የማያገለግል፣ በብልሹ አሰራርና ሌብነት ውስጥ የተዘፈቀ አመራር ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.