Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተሰጡ አቅጣጫዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በተያዘው በጀት ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
ኢኮኖሚው አካታችና የሕዝቡን ኑሮ የሚያሻሽል እንዲሆን ሰፊ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው ÷ በዚህም አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህም በቀደሙት ዓመታት ይመረት የነበረውን ሰብል በመጠን እና በአይነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በእንስሳት ሃብት ልማት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው÷ በተለይም በሌማት ትሩፋት የአሳ፣ የእንቁላል፣ የማርና የወተት ምርቶች የላቀ እድገት አሳይተዋል ብለዋል፡፡
ኢንዱስትሪ በሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት ላይ የነበረው ድርሻ በከፍተኛ ሀኔታ መጨመር መቻሉን ጠቁመው÷ የአገልግሎት ዘርፉ ዘመናዊ አሰራር እንዲላበስ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበው ገቢ መጨመሩን የገለጹት አቶ አደም÷ ቀደም ባሉት ዓመታት ከነበረው አንጻር በ2018 ሩብ ዓመት ብቻ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.