አምነስቲ ኢንተርናሽል ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው ዘገባ ስህተት መሆኑን ገልጾ ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አምነስቲ ኢንተርናሽል ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው ዘገባ ስህተት መሆኑን ገልጾ ይቅርታ ጠየቀ፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት ከሰሞኑ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለቆት የነበረው የቪዲዮ ይዘት የተሳሳተ መረጃ መሆኑን በማረጋገጥ ከገፆቹ ላይ ያነሳ ሲሆን የተሳሳተ መረጃ በማውጣቱም ይቅርታ ጠይቋል፡፡
ይኸው ድርጅት ግንቦት ወር ላይ 2012 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የማጣራት ተግባር በማከናወን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መንግስት ሕግ ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃዎች ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርጎ የማጠልሸት ዝንባሌ የሚስተዋልበት መሆኑን የሚገልፅ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዚህ መግለጫውም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በአብዛኛው ገለልተኘነት የጎደለው፣ የማስረጃ ምዘና ችግር ያለበት፣ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና ዐውድ ያላገናዘበ እና ሌሎችም መሰርታዊ ግድፈቶች ያሉበት እንደሆነ በመግለጽ ድርጅቱ ካወጣቸው ሪፖርቶችና በከፊል ተዐማኒነት ካላቸው ጉዳዮች መካከልም ቢሆን በርካቶቹ ጉዳያቸው በአምነስቲ ሪፖርቱ ከመውጣቱም በፊት በመንግስት ታውቀው የምርመራ ስራ ሲከናወንባቸው እንደነበር በመግለጽ በሪፖርት አዘጋጆቹ ዘንድ የፖለቲካ ወገንተኛነት እንደሚታይ አስታውቆም ነበር።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሳሳተ መረጃ በማውጣቱ ይቅርታ መጠየቁን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባወጣው መግለጫ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽል አይነት ትልቅ ድርጅት የአንድ ሀገርን ገጽታ ሊያበላሽ የሚችል ስህተት መስራትና ማሰራጨት ከድርጅቱ የማይጠበቅ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም ለወደፊቱ ተዓማኒነት የሌላቸው መረጃዎችን ከማሰራጨቱ በፊት ስለመረጃው ትክክለገኛነት ከሚመለከተው አካል ማጣራት ተገቢ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡