Fana: At a Speed of Life!

ልዩነቶች የዕድገት እንቅፋት መሆን የለባቸውም – አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ልዩነቶች ለጋራ ዕድገት እንቅፋት መሆን የለባቸውም አሉ፡፡

ልዩነቶችን የሚያቀነቅኑ አካላት ወደ ግጭት እንደሚያመሩ ጠቅሰው፤ ከግጭት የሚገኝ ፋይዳ እንደሌለም አስረድተዋል፡፡

የሃሳብ፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ሌሎች ልዩነቶች ልማትን የሚያደናቅፉ መሆን እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ በግጭት መጠፋፋት፣ ሃብት ንብረት ማውደም እና ሀገር ማጥፋት እንጂ የሚመጣ ውጤት የለም፡፡

ስለሆነም ሰከን ብሎ በማሰብ ልዩነቶችን ለዕድገት ምንጭ አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ልዩነትን የሚያቀነቅኑ ሰዎች መገንጠልንም እንደሚያስቡ አንስተው፤ መገንጠል ከትልቅ ወደ ትንሽ መውረድ ወይም ማነስ ማለት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የተገነጠሉ ሀገራት እስካሁን ድረስ ፍትህ እና ዴሞክራሲን ማምጣት እንዳልቻሉ ነው ያብራሩት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)።

አንድ ኃይል ከተገነጠለ በውስጡ የመገንጠል ሃሳብ ያላቸው ሌሎች ሃይሎች እንደሚነሱበት ገልጸው፤ ይህም የሚሆነው ያዩት፣ ልምምዳቸው እና ሥነ ልቦናቸው በመገንጠል እሳቤ የተቀረጸ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም መገንጠል ፋይዳ የሌለው እሳቤ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በብርሃኑ አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.