Fana: At a Speed of Life!

በውሃ ሃብት ላይ በትብብር መስራት ለልማትና ቀጣናዊ ውሕደት ቁልፍ መሳሪያ ነው – ቼይክ ቲዲያኔ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በትብብር ላይ ለተመሰረተ የውሃና ኢነርጂ ልማትና ለአፍሪካ መር መፍትሔዎች ስትራቴጂካዊ ሚና እየተወጣች ነው አሉ የአፍሪካ የውሃ ሚኒስትሮች ም/ቤት ፕሬዚዳንትና የሴኔጋል የውሃ ሚኒስትር ቼይክ ቲዲያኔ (ዶ/ር) ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሳይንስ ሙዚዬም የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አስጀምረዋል።
ቼይክ ቲዲያኔ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የስልጣኔ ምድር፣ የአፍሪካዊያን የማንነታቸው መገለጫና የመመካከሪያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በተደረገላቸው አቀባበል ትልቅ ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በርካታ አፍሪካዊያን አሁንም ድረስ የንጹህ መጠጥ ውሃና የታዳሽ ኃይል አቅርቦት እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሰው÷ በአህጉሪቱ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ወንዞች በርካታ ሀገራትን በማገናኘት ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም በትብብር ዘላቂ ልማት እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያነሱት ሚኒስትሩ ÷ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚጋሩ የአህጉሪቷ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ለትብብርና ለልማት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የውኃና ኢነርጂ ሳምንትን በማዘጋጀት በዘርፉ ያሉ ወርቃማ ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በመለየት አፍሪካ መር መፍትሔ መገንባት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ መድረክ መፍጠሯን አስረድተዋል።
በውሃ ሃብት ላይ በትብብር መስራት ለሰላም፣ ለልማት እና ቀጣናዊ ውህደት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአህጉሪቱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለጋራ ተጠቃሚነት በማዋል ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር፣ ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታን የማረጋገጥ ግብን ያነገበ ነው ብለዋል፡፡
በናይል ተፋሰስ የውሃ ሀብት ላይ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ድንበር ዘለል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ፣ ፀሀይ፣ ንፋስና የመሳሰሉት የታዳሽ ኃይል ሀብት ያላቸው ሀገራት ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ተሞክሮ በማስፋት ንፁህና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት የተፋሰሱን ሀገራትና የአህጉሪቷን ሕዝብ ብልፅግና ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.