Fana: At a Speed of Life!

በተያዘው ዓመት 9 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ስንዴ ይመረታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተያዘው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 5 እስከ 9 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ስንዴ ይመረታል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በምስራቅ ሸዋ ዞን የክረምት ስንዴ ምርት አሰባሰብ ሒደትን በመጎብኘት የበጋ ስንዴ ልማት ሥራን አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጉብኝቱን ተከትሎ በሰጡት ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምት ወራት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚጠጋ ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን ገልጸው÷ በበጋም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ከ8 ነጥብ 5 እስከ 9 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ ስንዴ እንደሚመረት ነው ያብራሩት።

ይህም ከአምናው ምርት አንፃር በእጅጉ የበለጠ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዞኑ ባደረጉት ጉብኝት ከስንዴ በተጨማሪ የሙዝ፣ ፓፓያ እና ዓሣ ምርቶች ማየታቸውን ገልጸው ÷ ለጤና፣ ገንዘብና ሀብት ለማግኘት እንዲሁም በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል የሚያግዙ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ150 ሺህ በላይ የውሃ ፓምፖች ወደ ስራ ገብተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በ10 ሺህ የሚገመቱ ትራክተሮችና 1 ሺህ ኮምባይነሮች ስራ ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ማሽን የማበራከቱ ጉዳይ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ÷ ፓምፕና ትራክተር ከውጭ ከማስገባት ባሻገር በሀገር ውስጥ ማቅረብ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ከፓፓያና ሙዝ ጋር በተያያዘ ባነሱት ሐሳብ ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት የምምረት ስራ እየተከናወነ እንደሆነና እነዚህን በምርምር በማሻሻል ከሄክታር የሚገኘውን ምርት የማሳደግ ስራ እንደሚከናወን እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእጅጉ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.