Fana: At a Speed of Life!

ፍትሕን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የዐቃቤ ሕጎች ሚና

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ ዐቃቤ ሕግ ፍትሕን ለማስፈንና የሕግ በላይነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል አሉ።
በቻይና ጓንጁ ከተማ የቻይና – አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ በጠቅላይ ዐቃብያነ ሕጎቻቸው እና ልዑካን ቡድኖቻቸው አማካኝነት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ የቻይና – አፍሪካ ትብብር ፎረም በአፍሪካ ሀገራትና በቻይና መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በኢኮኖሚ እድገት እና ሁሉንም ወገን ያከበረ ፖለቲካዊ አጋርነትን እውን በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ ሥርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
ፎረሙ በዚህ ወቅት መደረጉ ሀሳቦችን ለመለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዐቃቤ ሕግ ገለልተኛነቱን በማረጋገጥ እውነትን የማፈላለግ እና ፍትሕን የማስፈን ኃላፊነቱን በመወጣት ለተባበሩት መንግስታት ዘላቂ ልማት ግብ 16 መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክትም አመላክተዋል።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ እና ሕግ ጉዳዮች ኮሚሽን ጸሐፊ ቼን ዌንኪንግ በበኩላቸው÷ ፎረሙ የሕግ የበላይነት መከበር ለአንድ ሀገር መዘመን የሚኖረውን ገንቢ ሚና በመረዳት ጠንካራ ትብብር እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በቀጣይም ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት የእርስ እርስ ልምድ ልውውጦችን በማድረግ በጋራ አብረው መስራት እንደሚገባቸው መናገራቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.