በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር የሺመብራት መርሻ (ዶ/ር) መሾማቸው ሲሰማ ብዙዎች መቀበል ተስኗቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲውን ለመምራት በተሾሙበት ወቅት ቢሯቸው ስልክ የደወለ ሰው ሴት ፕሬዚዳንት እንደማይኖር በማሰብ “ፀሐፊው ነሽ?” የመባላቸውን ገጠመኝ አጫውተውናል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፂዮን ማርያም ቀበሌ የተወለዱት አምባሳደር የሺመብራት (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ከስኬታቸው ጀርባ ከልጅነት እስከ እውቀት ባህልና አመለካከት እንደፈተናቸው ተናግረዋል።
በአካባቢው በወቅቱ 8ኛ ክፍልን የተሻገረች ብቸኛ ሴት እንደሆኑና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተልም ደብረማርቆስ ንጉስ ተክለኃይማኖት ትምህርት ቤት እየተጓዙ መማራቸውን አስታውሰዋል።
መመህርነት እና ወታደር መሆን የዘውትር ምኞቴ ነው የሚሉት አምባሳደሯ÷ መመህርነት ጥሪያቸው ሆኖ ለትምህርት ሀረር ኮሌጅ መመደባቸውንም ገልጸዋል።
በሕይወታቸው ለተሻለ ስራና ውጤት የሚተጉት አምባሳደር የሺመብራት (ዶ/ር)÷ ከባሕር ዳርና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ባሻገር ባህር ማዶ ተጉዘው በዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉም አስረድተዋል።
ጠንካራ ሰራተኝነታቸው በብዙ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲታጩ ምክንያት የሆናቸው ሲሆን÷ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በቅድስት ዘውዱ
አምባሳደር የሺመብራት መርሻ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ይከታተሉ👇
https://www.youtube.com/watch?v=ESvfhjdsEso
 
			 
				