የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከጣልያን ጋር ያላትን ግንኙነት አሳድጓል – አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከጣልያን በተጨማሪ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አሳድጓል አሉ በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ፡፡
አምባሳደሯ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮ – ጣልያን ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰሩት ዲፕሎማሲያዊ ስራ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራችውና በጣልያን የነበረችው የፀሐይ አውሮፕላን ወደ ሀገሯ ተመልሳለች ነው ያሉት፡፡
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ዘርፎች እድገት አሳይቷል ያሉት አምባሳደር ደሚቱ÷ በዚህም በርካታ የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በኢንዱስትሪና ተሸከርካሪ ምርት፣ በጨርቃጨርቅና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በቡናና ግብርና ውጤቶች ሁለቱ ሀገራት በቅንጅት የሚሰሩባቸው መስኮች መሆናቸውን አመላክተዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ተሰሚነቷና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ማደጉን ጠቅሰው÷ ያለን የተፈጥሮ ሃብት እና የሰው ኃይል የውጪ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአቤል ነዋይ
 
			 
				