ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት ሮኬቶችን ተኮሰች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትሮች ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያዋስነውን አካባቢ እየጎበኙ በነበረበት ወቅት ሮኬቶችን ተኮሰች።
ሰሜን ኮሪያ በዚህ ሳምንት ከበርካታ የሮኬት ማስወንጨፊያ ስርዓቷ ወደ 10 የሚጠጉ ሮኬቶችን መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል፡፡
ሮኬቶቹ የተተኮሱት ወደ ምዕራባዊ የፓስፊክ ውቅያኖስ የውሃ ክፍል ሲሆን፥ ያደረሱት ጉዳት መጠን እየተጣራ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስትሮቹ ተናግረዋል፡፡
ሮኬቶቹ የተወነጨፉት የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሰትና የደቡብ ኮሪያ አቻቸው አህን ጂዩ ባክ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ በሆነው አካባቢ ካደረጉት ጉብኝት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በተመሳሳይ ከቀናት በፊት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሊ ጄ ምያንግ ከቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር በተገናኙበት የእስያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ወቅት የመድፍ ሮኬቶችን ተኩሳለች ሲል የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ከስሷል፡፡
በሶስና አለማየሁ