“ደብረታቦርን በደብረታቦር” በሚል የቡሄ በዓል ለ3ኛ ጊዜ በደብረታቦር ከተማ ይከበራል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደብረታቦር /ቡሄ/ በዓል ህዝባዊ ባህሉን፣ የቀደመ የአከባበር ታሪኩን በጠበቀ እና በተለየ መልኩ በደብረታቦር ከተማ እንዲከበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በነገው እለት የሚከበረውን የደብረታቦር /ቡሄ/ በዓል አስመልክቶ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቱ ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው በሰጡት መግለጫ፥ በዓሉ “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል ስያሜ በከተማዋ በተለየ መልኩ ይከበራል ብለዋል።
በደብረ ታቦር ከተማ 3ኛ ጊዜ የሚከበረው በአሉ ከተማዋን እንደመለያ በማድረግ የቱሪዝም ፍሰቱን ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
በበዓሉ ስያሜ ለምትጠራው ጥንታዊቷ የደብረታቦር ከተማ በዓሉ በዚህ መልኩ በከተማዋ መከበሩ የከተማዋን የጎብኚዎች ቁጥር በማሳደግ ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ አስተዋጾው የላቀ መሆኑን በመግላጫው አንስተዋል።
በተለይ የቡሄ በዓልና መሰል በዓላት የሰዎችን ግንኙነት ከፍ የሚያደርጉ በመሆኑ ወንድማማችነትን ለማጠናከር፣ አብሮ መኖርን ለማሳደግ፣ አንድነትን ለማጠናከርና ፍቅርንም ለማጎልበት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
በነገው እለት በሚከበረው የደብረታቦር በዓል የኮቪድ 19 ታሳቢ በማድረግ ትርዒቶች የማይኖሩ ይሆናልም ብለዋል።
በዓሉብ ዩኒቨርሲቲው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ ሙሁራን ጋር ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት በማድረግ ይከበራል ተብሏል።
የቡሄ በዓል ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባለፈ ህዝባዊ በዓል መሆኑ ይታወቃል።
በሃይማኖት ኢያሱ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።