Fana: At a Speed of Life!

የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) የተወለዱት ከአባታቸው አቶ ዴሌቦ ሸለሞ እና ከእናታቸው አሹሬ ደከጉ ግንቦት 1930 ዓ.ም በሀዲያ ዞን በቀድሞው አጠራር በሶሮ አውራጃ በኩፋና ቀበሌ ያሮ በተባለው መንደር ነው፡፡

ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) ገና የ13 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር በአንድ ሳምንት ውስጥ እናትና አባታቸውን ያጡት፡፡

በወቅቱም ብዙ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበርና ከሦስት ዓመት በኋላ በአንድ ዘመዳቸው እርዳታ ሆሳዕና ከተማ አካባቢ በሚገኘው ቦቢቾ የተባለ የሱዳን ኢንተርየር ሚሲዮን ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል በመግባት ትምህርታቸውን መጀመራቸው ይነገራል፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር እሳቸው ሁለተኛ ስሜ የሚሉት “ጌታሁን” የሚለው መጠሪያ የተሰጣቸው፡፡ በሁሉም የጥናትና ምርምር እንዲሁም የመጽሐፍ ስራዎቻቸው ላይ ወላጆቻቸው ካወጡላቸው ላጵሶ ከሚለው ስም ቀጥሎ ጌታሁንን በማሳጠር “ጌ” እያሉ ይፅፉት የነበረው፡፡

ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) በትምህርት ዘመናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ በታሪክና ንግግር ከፊት ከሚቀመጡ ተማሪዎች አንዱ እንደነበሩም ጽፈዋል፡፡

መደበኛ የትምህርት ዕድሜያቸው አልፎ ትምህርት መጀመራቸው በጨዋታ ሳይታለሉ ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል፡፡

ትምህርት ከጀመሩበት ቦቢቾ ሱዳን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ሆሳዕና ወደሚገኘው ራስ አባተ ቧ ያለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመዛወር የሰባትና ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውንም አጠናቅቀዋል፡፡

በዚህም ወቅት በየሳምንቱ በሚደረግ የክርክር ውድድር አሸናፊ በመሆን በወቅቱ የአውራጃ አስተዳዳሪ ከነበሩ ግለሰብ እጅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከ1953 እስከ 1956 ያለውን የትምህርት ዘመን ደግሞ አዳማ ወደሚገኘው አፄ ገላውዲዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በመዛወር ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

በአዳማ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት በሳምንቱ መጨረሻ አርብ ጀምሮ እስከ እሁድ ባለው ጊዜ እንዲሁም በክረምቱ ጊዜ እስከ ወንጂ ድረስ በመሄድ የወንጌል ትምህርትን ለሰራተኞች ያስተምሩ ነበር፡፡ ቆይተውም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ አጠገብ በዓለም ጤና ከተማ ቤተክርስቲያንና የግል ትምህርት ቤት አሰሩ፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከ1957 እስከ 1958 ዓ.ም ድረስ በቤተክርስቲያኑና የግል ትምህርት ቤቱ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በ1958 ዓ.ም ከሜኖ ናይት ኮሌጅ የተሰጣቸውን ነፃ የትምህርት እድል ለመከታተል ወደ አሜሪካን ሀገር ቨርጂኒያ ግዛት የተጓዙ ሲሆን÷ ከሜኖናት ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ትምህርቸውን በመቀጠልም በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በ1963 ዓ.ም በታሪክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ በዛው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመቀጠል በ1966 ዓ.ም በታሪክና ፍልስፍና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በአሜሪካ ቨርጂንያ ዩኒየን ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ የአፍሪካ ጥናት ክፍል ኃላፊና የታሪክ አስተማሪ ሆነው በ1967 ዓ.ም መስራት ጀመሩ፡፡

በ1968 የእናት ሀገር ጥሪን ሲሰሙ ግን ስራቸውን በፈቃዳቸው አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን÷ በሀገራቸውም በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በባህል ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥና በሌሎች በርካታ ቦታዎች በባለሙያነት ሰርተዋል፡፡

ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) ከልጅነታቸው ጀምሮ የታዘቡት የመሬት ስሪት አንዱን ገፍቶ ሌላውን ማቀፉ ለታሪክ ጥናት እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡

ላጲሶ (ፕ/ር) በህይወት ዘመናቸው በርካታ የታሪክ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን ታሪክ በመጽሐፍ መልክ በማቅረብ ለአንባቢ አድርሰዋል፡፡

በመጽሐፍ መልክ ካቀረቧቸው ውስጥም የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም፣ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥት ታሪክ፣ የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች (ታሪክ)፣ የቀይ ባሕርና የዓባይ ሸለቆ ሚና፣ የምፅዋ ሲምፖሲየም-1974፣ የኢትዮጵያ የመከራ ሥርዓትና የኤርትራ ጥያቄ፣ የምርትና የባህል ዘመቻ በከምባታና ሀዲያ አውራጃ እንዲሁም የአዲስ አበባ መዲና እድገትና ሚና በኢትዮጵያ ታሪክ የሚሉና ሌሎች ይገኙበታል።

በታሪክ ጥናትና ምርምራቸውም ሳይንስ በየጊዜው እየደረሳቸው ታሪክ ማጥኛ መንገድ ይሆናሉ ብሎ ያረጋገጣቸውን መንገዶች ሁሉ በመጠቀም የሀገር ታሪክ እንዲታወቅ አድርገዋል፡፡ ከመጽሐፋቸው በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አስተምረዋል፡፡

በጽሑፉ ውስጥ ያሉ መረጃዎች በዋናነት የተገኙት በ1982 ዓ.ም ካሳተሙት ‘የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግስት ታሪክ’ ከሚለው መጽሐፋቸው ነው።

የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) በትናንትናው ዕለት ባደረባቸው ሕመም ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ 87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የአስከሬን ሽኝትና ቀብር ሥነ ሥርዓትም በነገው ዕለት ሕዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

በታምሩ ከፈለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.