90ኛው የአየር ኃይል የምስረታ በዓል በመጪው ህዳር 21 ይከበራል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 90ኛው የኢፌዴሪ አየር ኃይል የምስረታ በዓል በመጪው ህዳር 21 በተለያዩ መርሐ ግብሮች በቢሾፍቱ ከተማ ይከበራል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ሰጡት እንዳሉት፥ አየር ኃይልን ኢትዮጵያን በሚመጥን ደረጃ ለማቆም በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከአፍሪካ ሀገራት ቀድማ መታጠቋን ያስታወሱት ዋና አዛዡ፥ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት በመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ዓለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ ይህን ሁነት በተገቢው ሁኔታ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም ወደ ከተማዋ የሚመጡ ተሳታፊዎችን በተሟላ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
የምስረታ በዓሉን በማስመልከት “ለአየር ኃይል በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
አየር ኃይል ምሩጽ ይፍጠርን የመሰለ ሀገርን ያስጠራ አትሌትን ማፍራት መቻሉን ያስታወሱት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን፥ በውድድሩ ከሀገር ውስጥና ከውጭ 25 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም