በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሱ ሰብሎች ተሰብስበዋል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ እንደሻው ጀማነህ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያየ አዘዕርት ተሸፍኗል፡፡
ከዚህም ውስጥ እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ከ820 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተሰበሰቡ ሰብሎች መወቃታቸውን የገለጹት ኃላፊው፥ 23 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የደረሱ ሰብሎች የተሰበሰቡባቸውን መሬቶች ለበጋ የመስኖ ልማት ለማዋል የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በአመት ሶስት ጊዜ ለማምረት የያዘው እቅድ በአበረታች ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፥ እየለሙ ያሉ የእርሻ መሬቶች በየዓመቱ እየጨመሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ሳይባክኑ በጥንቃቄ የመሰብሰቡን ስራ በትኩረት እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡
በአቤል ነዋይ