አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር አኩሪ ታሪክ አለው – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር አኩሪ ታሪክ ያለው ነው አሉ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።
90ኛ ዓመት የአየር ኃይል የምስረታ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ከአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉት ዋና አዛዡ፤ አየር ኃይል ብዙ ጀግኖችን ያፈራ አንጋፋ የአቪዬሽን ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ አኩሪ ታሪክ እንዳለው ገልጸው፤ የአየር ኃይልን ሙሉ ዝግጁነት ህዝባችን እንዲያውቀውና የፈጠረውን አቅም እንዲረዳው ለማድረግ የምስረታ በዓሉ ይከበራል ብለዋል።
በመሆኑም ማህበረሰቡ በዓሉን በጋራ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ የመከላከያ ሠራዊታችን የሀገራችን ሰላም ዋስትና የህዝባችን መከታና መኩሪያ ኃይል ነው ብለዋል።
አየር ኃይሉ የሚያከብረው 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የህዝቡ በዓል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአዳማ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎች በዓሉን በጋራ እንደሚያከብሩ ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
90ኛ ዓመት የተቋሙ የምስረታ በዓል ‘የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት’ በሚል መሪ ሀሳብ በአቪዬሽን ኤክስፖ፣ በፓናል ውይይት እና በዓይነቱ ለየት ባለ የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት እንዲሁም በበርካታ ዝግጅቶች ይከበራል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ለሠራዊቱ ያለውን ክብር ለመግለፅ ስጦታ አበርክቷል።