በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን የመተግበር ግዴታ አለባቸው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ሁሉም ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን የመተግበር ግዴታ አለባቸው አሉ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሪፎርሙ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን በሚፈለገው ልህቀት ያስቀጥላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የመደመር መንግሥት ዕይታ ለዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው ስልጠና ወቅት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ተቋማት ዘመናትን የሚሻገሩ ዘላቂና እኛን መምሰል አለባቸው በሚል በግልጽ መቀመጡን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሪፎርሙ በሀገራዊ ዕሳቤ የተቃኘ፣ ከሀገራዊ እሴት የተቀዳ መሆኑን አመልክተው፤ በሁሉም ተቋማት ገቢራዊ የሚደረግ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሪፎርሙ በሦስት ምዕራፎች ሲከፈል የተሻለ አፈፃፀም፣ መካከለኛና ወደኋላ የቀሩትን በመለየት መሆኑን አንስተው፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግቦ በግልጽ ተመርጧል ነው ያሉት።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ በሶስት ምዕራፍ የተለየበት ሌላው መንገድ ተቋማት ከመጀመሪያዎቹ ልምድ እየወሰዱ በተሻለ መፈፀም እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ሂደቱ በሰባቱ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ምሰሶዎች አኳያ የሚታይ በመሆኑ ተቋማት ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዘመናት መካከል የፀና ተቋም የመገንባት ዓላማ የያዘውን ሪፎርም በሂደት ማሻሻልና ማሳለጥ ይገባል ብለዋል።
በዚህም የመጀመሪያ ምዕራፍ ተቋማት ወደ ትግበራ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ያሉት ደግሞ ወደ ዝግጅት በፍጥነት መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለሪፎርሙ ስኬት ምቹ የሥራ ቦታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የሰራተኛው ምዘና ከሥራው ዓይነትና ባህርይ ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ተቋማት የሰራተኞችን አቅም ለመለየት፣ ለመመዘንና ለማብቃት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚከተለው አሰራር ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምዘና ወቅት ስራውን በአግባቡ ሳይረዳ የሚሰራ ባለሙያ እንዳለ ጠቅሰው፤ ምዘናው የሰራተኛውን ጉድለቶች ለይቶ መሙላት ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል።