ከተማ አስተዳደሩ ሀገራዊ ዕቅዶችን ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራቱን ይቀጥላል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቀመጡ ሀገራዊ ዕቅዶችን ለማሳካት በትጋትና በቁርጠኝነት መስራቱን ይቀጥላል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ ከከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር “በመደመር መንግስት እይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የተሰጠውን ስልጠና ለመተግበር የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል፡፡
ውይይቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም÷ እንደ ከተማ አስተዳደር የተያዙ ግቦችን ለማሳካት በጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ እና ፍጥነት መርህ ግቦቹን ለማሳካት የተዘጋጀውን ዝርዝር እቅድ የጋራ አድርገናል ብለዋል።
ከተለዩት ዋና ዋና ግቦች መካከል የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባን፣ የ5 ሚሊየን ኮደሮች ሥልጠናን፣ የተጀመሩ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቶችን፣ ለምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ግቦችን ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ ሌብነት፣ ጉቦኝነትንና ብልሹ አሰራርን፣ በመንደርተኝነትና በአካባቢዊነት ማሰብና መስራትን እንዲሁም ጠባቂነትን መቀነስ፣ ተረጂነትንና ልመናን፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን መከላከል የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን መከላከል እና ሰላማዊ ሁኔታን የሚያውኩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የዋና ዋና ግቦች የትኩረት ማዕከል ሆነው የሚፈፀሙ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ግቦቹን ለማሳካት እንደ ወትሮው ትውልድና ተቋምን በመገንባት ከተማ አስተዳደሩ በትጋትና በቁርጠኝነት አንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡