Fana: At a Speed of Life!

የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ አስችሏል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ብሩህ ተስፋ የፈነጠቁ ትልልቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ፡፡

10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል መሪ ሃሳብ በሰመራ ሎጊያ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

እንደ ሀገር የተያዙ የልማት ግቦች እና ትልሞች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስችልም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቁመው ÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ብሩህ ተስፋን የፈነጠቁ ትልልቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ሥራዎች ለአፍሪካ በሞዴልነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንና የተመዘገቡ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ቀሪ ሥራዎች ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በመንግስት የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመተግበር ለላቀ ስኬት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በፎረሙ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዛህራ ሁመድ፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በቤዛዊት ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.