ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኮምቦልቻ ከተማን ሰው ተኮር ተግባራት አደነቁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኮምቦልቻ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር ተግባራት እና ዘመናዊ አገልግሎቶች የሚደነቁ ናቸው አሉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር ዲጂታላይዝድ ዘመናዊ ህንጻ የእድሳት ሂደትን ተመልክተዋል።
በምልከታቸውም ከተማ አስተዳደሩ ለዘመናዊ አገልግሎት እና ለሰው ተኮር ተግባራት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ህንጻ ዲጂታላይዝድ አሰራርን ለመተግበር በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን አጋዥ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የህንጻ እድሳቱ የስማርት ሲቲ እሴቶችን ያሟላ ሲሆን ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ለሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የከተማ አስተዳደሩ በ43 ሚሊየን ብር ወጪ ባስገነባቸው ሁለት የመኖሪያ ህንጻዎች ላይ የሚገኙ 36 ቤቶችን በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ አስረክበዋል።
ቤቶቹን ከማስረከብ በተጨማሪ የምግብ ቁሳቁስም አበርክተዋል።
በለይኩን ዓለም