በሩብ ዓመቱ ከ545 ሺህ በላይ ፓስፖርት ለዜጎች ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አለ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን የ2018 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት÷ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 545 ሺ 491 ፓስፖርት ለዜጎች ተደራሽ ተደርጓል።
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት (ኢ-ፓስፖርት) ደግሞ 14 ሺህ 818 ለሚሆኑ አገልግሎት ፈላጊዎች ተደራሽ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሀሰተኛ ፓስፖርት ይዘው የተገኙ የሀገር ውስጥና የውጪ ዜጎች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን አብራርተዋል።
በሩብ ዓመቱ 860 ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው ፖስፖርት ለመውሰድ የሞከሩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን ገልጸዋል።
በድንበር አካባቢ በተከናወነ የቁጥጥር ሥራ 16 ሺህ 465 የሚሆኑ የውጭና የሀገር ውስጥ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡና ከኢትዮጵያ ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል።
በተቋሙ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ከተገልጋዮች የሚነሱትን ጥያቄዎች በሟሟላት በመደበኛ በስድስት ወር ይሰጥ የነበረውን ፓስፖርት በሁለት ወራት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ ወጥነትን በመከላከል ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ በበኩላቸው÷ አገልግሎቱ የዲጂታል አሰራር ሥርዓትን በመከተል መስጠት የጀመረውን አገልግሎት ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ፣ ቅርንጫፎቹን ማስፋፋት እንዲሁም ተቋማዊ ደህንነት ለማጠናከር የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ ማጠናክር እንደሚኖሩበት አስገንዝበዋል።