በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ የወጣቶችን ሃሳብ በማገዝ ለሀገር ጥቅም ማዋል ይገባል – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018(ኤፍ ኤም ሲ) ወጣቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የሰሩትን እና ያሰቡትን በማገዝ ለሀገር ጥቅም እንዲውል መስራት ይገባል አሉ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)።
ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዋና ጽ/ቤቱን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት÷ በኢንስቲትዩቱ ባለፉት 5 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ውጤት የተገኘባቸው ሥራዎች ተከናውነዋል።
አዲሱ ዋና ጽ/ቤት ላይ የዘርፉ ሥራዎች በሰፊው መጀመራቸውን ገልጸው÷ አሁን ላይ የተገነቡ 5 ሕንጻዎች እና የታደሱ 2 ሕንጻዎች መኖራቸውንም አብራርተዋል፡፡
ባለ 15 ወለል ሕንጻ የሆነው ዋና ጽ/ቤቱ በውስጡ ያሉት የውኃ፣ መብራት፣ መስኮት እና ሌሎች ክፍሎች ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተምረው እና ተረድተው እንዲበቁ ለማድረግ በአጭር ኮርስ፣ በማስተርስ እና በፒኤችዲ ደረጃ ተምረው እንዲወጡ እና ዘርፉን እንዲያግዙ ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁሉንም ዘርፎች የሚነካ እና ሥራዎችን የሚያቀላጥፍ እንደሆነ ጠቁመው÷ በግብርና እና ጤና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ገብቶ በርካታ ስራዎችን እየቀነሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአጠቃላይ ሰውን የሚተካ ሳይሆን የሰውን ፍጥነት እና ምርታማነት የሚጨምር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እንዲሁም ክላውድ ዳታ ሴንተር ለመንግስት እና ለግል ተቋማት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ማሽን ቋንቋዎችን ተረድቶ እንዲሰራ በማድረግ ረገድ በ5 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛ ላይ ስራው መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም ድምጽን ወደ ጽሑፍ በመቀየር በጠቅላይ ፍ/ቤት እና ሌሎች ተቋማት ላይ ጥቅም ላይ በማዋል ሕብረተሰቡ በቀላሉ የፍርድ ሒደቱን በጽሑፍ እንዲያገኝ በማድረግ እንግልትን እያስቀረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወጣቶች ሃሳቦቻቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የስልጠና፣ የገንዘብ፣ የቦታ እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚፈልጉ እና አሁን ላይ ወደ 200 የሚሆኑ ስታርትአፖች እንዲካተቱ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም ወጣቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰሩትን እና ያሰቡትን በማገዝ እውን እንዲሆንና ለሀገር ጥቅም እንዲውል መስራት ይገባል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!