የሃገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል የመንግስትን የደህንነት ሚስጥር በውጭ ላለ የሽብር ቡድን አሳልፈው በመስጠት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ህውሃት ፅህፈት ቤት የቀድሞ ሃላፊ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ፣ የህግና ፍትህ ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም ይደጉ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የደህንነት ሃላፊ አቶ አጽብሃ አለማየሁን ጨምሮ አምስት ተጠርጣሪዎች ዛሬ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሃገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል የመንግስትን የደህንነት ሚስጥር በውጭ ላለ የሽብር ቡድን አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው ምርመራ ሲደረግባቸው የነበሩ ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ የተጠረጠሩበት ወንጀል የሽብር ወንጀል በመሆኑ ስልጣን ላለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት መመለሱን ተከትሎ ነው ዛሬ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት በተጠረጠርንበት ወንጀል ተመርምሮ የወንጀል ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ታይቶ የቀረበ ማስረጃ የለም ስለዚህ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም የሚሉ መቃወሚያ አንስተዋል።
ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ ያስገባው የከፍተኛ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ተረኛ ችሎት ለተጨማሪ ምርመራ ለመርማሪ ፖሊስ የ10 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
ውጤቱን ለመጠባበቅም ለነሃሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን በ23 የስራ ቀን ባለመሆኑ ቀደም ብሎ በ22 እንዲታይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር ወንጀል የተጠረጠሩ በሁለት መዝገብ የተከፈሉ አጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ህግ እንደመዝገባቸው በ10 እና በ15 ቀናት ወስጥ ክስ እንዲመሰርትባቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት በልደታ አዳራሽ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በእነ አረፋት አቡበከር መዝገብ 9 ተጠርጣሪዎች እና በአዲሱ ቶሎሳ መዝገብ ደግሞ 5 ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ 14 ሰዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ ያካሄደውን የምርመራ መዝገብ ማጠናቀቁን ገልጿል።
ዐቃቤ ህግ በህጉ መሰረት የክስ መመስረቻ 15 ቀን ይሰጠኝ ስትል ፍርድ ቤቱን ጠይቃለች።
በጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ተሳትፎ እንደሌላቸው እና በእለቱ የሃጫሉን ለቅሶ ለመድረስ መሄዳቸውን ገልጸው ፍርድ ቤቱ ዋስ ሊፈቅድልን ይገባል ሲሉ የዋስትና ጥያቄ አንስተዋል።
ጠበቃቸውም በተመሳሳይ መዝገቡን ፖሊስ ማጠናቀቁን ገልጾ በምርመራው ደግሞ በእለቱ የተጠረጠሩት በእርስ በእርስ ግጭት መፍጠር እንጂ በተጠረጠሩበት ወንጀል የጠፋ የሰው ህይወት መኖሩ አልተገለጸም ስለዚህ የዋስትና መብታቸውን የሚከለከል አይደለም ሲል ተከራክሯል።
የባንክ ሂሳባቸው እንደታገደባቸው የገለጹት 3 ተጠርጣሪዎች ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸው የሂሳባቸው እግድ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሀግ በበኩሏ የዋስትና ጥያቄያቸው ላይ መቃወሚያ አንስታለች።
በወንጀለኛ መቅጫ ሰነ ስርአት ህጉ አንቀዕ 63 መሰረት ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ቢከሰሱና ጥፋተኛ ቢሆኑ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከ15 አመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ ይህ ደግሞ ዋስትና አያሰጥም ስለዚህ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ይደረግልኝ ስትል አመልክታለች።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድቤቱ በእነ አረፋት አቡበከር መዝገብ በተጠቀሱ 9 ሰዎች ላይ ለክስ መመሥረቻ 15 ቀን ሲሰጥ በአዲሱ ቶሎሳ መዝገብ ደግሞ 5 ተጠርጣሪዎች ላይ በ10 ቀን ውስጥ ዐቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረት አዟል።
በእነዚህ በተሰጡ በሁለቱ መዝገቦች ላይ በተሰጠው ጊዜ ዐቃቤ ህግ ክስ ካልመሰረተ እንለቀቅ የሚል አቤቱታ ማቅረብ ትችላላቹ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ