የወቅቱ ሃያላን ክለቦች ተጠባቂ ፍልሚያ…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ5ኛ ዙር መርሐ ግብር የወቅቱን ሃያላን ክለቦች አርሰናል እና ባየርን ሙኒክ የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ትኩረትን ስቧል፡፡
ሁለቱ ክለቦቸ በውድድር ዓመቱ በሻምፒየንስ ሊጉ ያደረጓቸውን አራቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል።
መድፈኞቹ ከዛሬው ጨዋታ አስቀድሞ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጉት የሰሜን ለንደን ደርቢ የከተማ ተቀናቃኛቸውን ቶተንሃም ሆትስፐር ሲያሸንፉ፥ ባቫሪያኑ በአንጻሩ በቡንደስሊጋው ፍሬቡርግን በማሸነፍ ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ማስቀጠል ችለዋል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል ዘጠኙን አሸንፎ በሁለቱ አቻ የተለያየ ሲሆን፥ በ29 ነጥብ ከተከታዩ ቼልሲ በስድስት ነጥብ በመራቅ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል፡፡
በውድድር ዓመቱ በሁሉም ውድድሮች አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው የቪንሰንት ኮምፓኒው ባየርን ሙኒክ በበኩሉ ቡንደስሊጋውን እየመራ ይገኛል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በአህጉራዊ ወድድሮች እጅግ ውጤታማን ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ዛሬ ምሽት እርስ በርስ የሚያደርጉት ፍልሚያ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ትኩረት ስቧል፡፡
በባየርንሙኒክ እጅግ አስደናቂ ጊዜን እያሰለፈ የሚገኘው እንግሊዛዊ ሃሪ ኬን አርሰናልን በገጠመባቸው 15 ጨዋታዎች 21 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፥ በምሽቱም ጨዋታ በተለይም ለመድፈኞቹ የተከላካይ መስመር ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በክሪስታል ፓላስ ቤት ቆይታቸው ስኬታማ ጥምረት የነበራቸው የባየርን ሙኒኩ ሚካኤል ኦሊሴና የአርሰናሉ ኤቤሬቼ ኤዜ ዛሬ ምሽት በተቃራኒ ይፋለማሉ፡፡
በባየርን በኩል ኮሎምቢያዊው ሊውስ ዲያዝ በቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ሲሆን፥ ፈረንሳዊው ሚካኤል ኦሊሴ በምሽቱ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች የዘንድሮውን የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያሸንፋሉ በሚል ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሁለቱ ክለቦች በሻምፒየንስ ሊግ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስ በርስ ጨዋታዎች ባየርን ሙኒክ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲሆን፥ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በመድረኩ በአጠቃላይ ከተገናኙባቸው 14 ጨዋታዎች ባየርን ሙኒክ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ፥ አርሰናል በሦስቱ ድል ቀንቶታል፡፡
ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን፥ አሳማኝ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ዛሬ ምሽት አስደናቂ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ምሽት 5 ሰዓት በኤሚሬትስ ስታዲየም የሚደረገውን የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ የ44 ዓመቱ ጣሊያናዊ ማርኮ ጉይዳ በመሃል ዳኝነት ይመሩታል፡፡
በአቤል ነዋይ