Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ያለ ደረሰኝ በሚንቀሳቀሱ 997 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ያለ ደረሰኝ በሚንቀሳቀሱ 997 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል አለ የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ፡፡

የቢሮው ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ የተሽከርካሪዎችን የህግ ተገዥነት ግንዛቤ ለማሻሻል እና የመዲናዋን የገቢ አቅም ለማሳደግ የቁጥጥር ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ ነው።

በዚህም በበጀት ዓመቱ በ5 ሺህ 203 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰኝ ቁጥጥር በማካሄድ ከ954 ሚሊየን ብር በላይ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ተደርጓል ብለዋል።

የደረሰኝ ቁጥጥሩ ወደ ከተማዋ በሚገቡ፣ ከከተማዋ በሚወጡና በከተማዋ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ሚኒባሶችና አነስተኛ ሽፍን መኪኖች ላይ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቁጥጥሩ ያለደረሰኝ ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 907 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ሲያዙ፤ 1 ሺህ 39 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ እንዲቆርጡ መደረጉን እንዲሁም በ997 ግብር ከፋዮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በቀን ከሚደረገው ቁጥጥር በተጨማሪ በሌሊትም ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው÷ ያለደረሰኝ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ህገ ወጥ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.