የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በግማሽ በጀት ዓመት 52 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከኢነርጂ ሽያጭና ከልዩ ልዩ ገቢ 52 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ሰብስቤያለሁ አለ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በሰጡት መግለጫ፥ ባለፉት ስድስት ወራት 266 ሺህ 916 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የተቋሙ አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር ከ5 ነጥብ 46 ሚሊየን መሻገሩን ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት 94 ነጥብ 8 በመቶ የአገልግሎቱ ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን በዘመናዊ የክፍያ አማራጮች የሚከፍሉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ባለፉት ወራት ከ52 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት የማሻሻያና መልሶ ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡
አገልግሎቱ በግማሽ በጀት ዓመቱ የኢነርጂ ሽያጭና የአዲስ ደንበኛ መስተንግዶን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ገቢ 52 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸው፥ ይህም የዕቅዱን 96 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመሰረተ ልማትና ንብረት ስርቆትና ውድመት ባደረሱ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ በፍርድ ቤት የገንዘብ መቀጮና የእስራት ቅጣት እንደተላለፈባቸው አንስተዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ