Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በቁርጠኝነት ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረሪ ክልል የተጀመሩ ሰው ተኮር ተግባራትን በማስፋት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።

በክልሉ “በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ሁለተኛ ዙር ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማጠናቀቂያ መድረክ ላይ እንዳሉት÷ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ዘርፉን ገበያ መር ለማድረግ ይሰራል።

በተለይ የእንስሳት ሃብት ልማትና አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የግብርና ሽግግር፣ የመሰረተ ልማት እና ማሕበራዊ ልማትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ ይህንን በማሟላት የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ማህበረሱቡ ለሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ምልከታ በመቀየር የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነት ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በዚህም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተለይ በሆቴል ኢንዱስትሪ ለሚሰማሩ አልሚዎች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።

በከተማ ልማት ዘርፍ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በማስፋት ዘላቂና ተቋማዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ በማሕበረሰቡ ዘንድ የወንድማማችነት መንፈስን በማጎልበት ሰላምን ማስፈንና ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓትን መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተስፋዬ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.