ከ30 ዓመታት በላይ በምርምር ስራ ያሳለፉት አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገራት በርካታ ውጤታማ የምርምር ሰራዎችን የሰሩ አንጋፋ ተመራማሪ ናቸው አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)።
አፈወርቅ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ ከ30 ዓመታት በላይ በምርምር ስራ ላይ አሳልፈዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን እሰራ ወረዳ በሚገኝ የገጠር መንደር ተወልደው ያደጉት አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) የልጅነት ጊዜያቸው ውጣውረድ የበዛበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በተወለዱበት አካባቢ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስላልነበረ ከሚኖሩበት አካባቢ 40 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ስንቅ ቋጥረውና ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ ለማወቅ ከተወለዱበት ቦታ 120 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደ ምትገኘው ጅማ ከተማ መጓዝ ነበረብኝ ይላሉ፡፡
ጅማ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ያየሁባት እና የተሳፈርኩባት፣ ኮካ የጠጣሁባት፣ ፎቅና መብራት ያየሁባት ለእኔ የቴክኖሎጂ ከተማ ናት ሲሉም በፈገግታ ያስታውሳሉ፡፡
ከዛም ለከፍተኛ ትምህርት አስመራ ዩኒቨርሲቲ መመደባቸውን በማረጋገጥ ጉዟቸውን ወደ አስመራ ከተማ በማድረግ ለአንድ ዓመት ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ሻቢያና ደርግ ጦርነት ላይ የነበሩበት ወቅት ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመዘዋወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጅ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ተመራማሪነት ሥራቸውን የጀመሩት አፈወርቅ (ፕ/ር)÷ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመዛወር ከሲኒዬር ተመራማሪነት እስከ ምክትል የዩኒቨርሲቲ ዲን በመሆን አገልግለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአርማዎር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በዋና ዳሬክተርነት ሀገራቸውን በማገልገል ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰሩ÷ የመመራመር ፍላጎታቸው በተግባር መገለጽ የጀመረው የዶሯቸውን እድሜ ስንት ሊሆን እንደሚችል የማወቅ ፍላጎት ባደረባቸው የልጅነት ጊዜ ሳይሆን እንዳልቀረ ያስታውሳሉ፡፡
የእሳቸው አበርክቶ በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም በርካታ ውጤታማ የምርምር ውጤቶችን ከማሳተም ጀምሮ በተለያዩ የስራ ተልዕኮዎች በጃፓንና በአሜሪካ አገልግለዋል፤ በምርምር ስራዎቻቸውም በርካታ እውቅና ተችሯቸዋል፡፡
አፈወርቅ (ፕ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ካገኟቸው እውቅናዎች መካከል በጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር የተበረከተላቸው የንጉስ ሽልማት ለአብነት ይጠቀሳል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው
አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ይከታተሉ👇
https://www.youtube.com/watch?v=Is8aYaFkzUU