Fana: At a Speed of Life!

ከ100 ቢሊየን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊየን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው÷ በቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶችና ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር በሚባሉ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተባባሪ ተቋማት ዙሪያ ጥናትና ክትትል ሲከናወን ቆይቷል፡፡

ፈቃድ ያላቸውና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በገቡት ውል መሰረት የማይሠሩ፣ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው እንዲሁም ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በስፖርት አወራራጅነት ተሰማርተው የነበሩ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ትስስር አማካይነት በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው መገኘታቸው ተገልጿል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር አማካኝነት 24 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አስታውቋል፡፡

በተለይ በሕጋዊነት ሽፋን ፈቃድ ያወጡት ድርጅቶች ላይ ክትትል ለማድረግ ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሁሉም ፈቃድ ሲያወጡ ይዘውት ከነበረው ቢሮ መልቀቃቸውና አድራሻቸውን መሰወራቸው ተረጋግጧል፡፡

የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ስርዓቶችን ከሚያሳልጡላቸው የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር በአጠቃላይ ሲያንቀሳቅሱት ከነበረው የገንዘብ መጠን መንግሥት በተለያዩ የገቢ አማራጮች ማግኘት የነበረበትን 100 ቢሊየን ብር በላይ መሰወራቸው እንደተደረሰበት አመላክቷል፡፡

የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በተለያዩ የገንዘብ ክፍያ ስርዓቶች አማካይነት የሚሰበስቡትንና የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን ያማከለ ግብር አለመክፈላቸው እንደተደረሰበት የጠቆመው መግለጫው÷ በክሪፕቶከረንሲ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ገንዘብ ማስተላላፊያ አማራጮች አማካኝነት የሚያገኙትን ገቢ በውጭ ምንዛሪ በመቀየር ሲሰውሩና ከሀገር እንዲወጣ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡

ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የሀገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፤ የደንበኛን ምስጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን የገንዘብ መጠን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈፃሚ ተቋማት በመደበቅ ወይም አሳንሶ በማቅረብ በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የሀገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የአገልግሎቱ መግለጫ አብራርቷል፡፡

የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ገለሠቦች ጭምር ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችው ውክልና በመስጠት ሕገ-ወጥ ድርጊቱን ሲፈጸሙ መቆየታቸው እንዲሁም ውጭ ሀገር የበለጸጉ ሶፍትዌሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውና ድርጅቶቹ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ ወንጀሉን ውስብስብና ለቁጥጥር አስቸጋሪ አድርጎት ቢቆይም የደኅንነት ተቋሙ ከሌሎች የመረጃና የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ባደረጉት ስምሪት ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸው ተመላክቷል፡፡

በሕገ ወጥ ድርጊቱ ከሀገር ሲሸሽ የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ ሽብርተኝነትንና ጸረ ሰላም ቡድኖችን በገንዘብ ለመደገፍ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል እንዲሁም ለኮንትሮባንድ ንግድ ማካሄጃ እንደሚውል የጠቆመው መግለጫው፤ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በመጻረር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ስጋት ላይ ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል በመሆኑ ዜጎች ማንኛውም አይነት ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ሲመለከቱ ለደኅንነትና ጸጥታ አካላት የሚሰጡትን ጥቆማ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.