አፍሪካ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ዕድገቷን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ናት – አቶ ቴዎድሮስ ምህረት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ልማትና ዕድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች አሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት።
4ኛው የአፍሪካ ህገመንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም ‘ህገ መንግሥታዊነት እና ሀገረ መንግሥት ግንባታ’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት፤ አፍሪካ ለሕገ-መንግሥታዊነት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ ማስቀጠል ይኖርባታል ብለዋል፡፡
አፍሪካ ቁልፍ የሕዝብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ የተረጋጋ ተቋማትን በመገንባት እና ተቋማዊ በማድረግ ረገድ በስፋት መስራት እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል፡፡
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና የሰብአዊ መብቶችን ለማጠናከር የአስተዳደር ሁኔታን ከማሻሻል ባሻገር የአህጉሪቱን ልማት ማፋጠን መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የዚምባብዌ ጠቅላይ ዳኛ እና የአፍሪካ የሕገ መንግሥት የዳኝነት አካላት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሉክ ማላባ በበኩላቸው÷ አፍሪካውያን በራሳቸው መተማመንና የለውጥ አጀንዳቸውን መምራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረትን መሠረታዊ መርሆች ማስጠበቅ እና አፍሪካውያን የራሳቸውን የለውጥ አጀንዳዎች መምራት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡