ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አካል መሆን አለባት – ጄነራል ፒየር ሺል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሣይ የምድር ኃይል አዛዥ ጄነራል ፒየር ሺል ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አካል መሆን አለባት አሉ።
ከቀናት በፊት በሁለትዮሽ ወታደራዊ ጉዳዮች ከመከላከያ ሠራዊት ጄነራል መኮንኖች ጋር የመከሩት ጄነራል ፒየር ሺል የተለያዩ ተቋማትን ጎብኝተው ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተዋል።
ጄነራል ፒየር ሺል ከመከላከያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በጣም ትልቅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ ኃይልና ሕዝብ አላት ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግዷን ለማቀላጠፍ እንድትችል የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አካል መሆን አለባት ነው ያሉት።
ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ሀሳብ እንደምትደግፍ ገልጸው፤ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ብዙ ድርጅቶችንም ሀሳቡን እየደገፉት መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ለማሻሻል እንደምትፈልግ ገልጸው፤ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው የዚህ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
በወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በሠላም ማስከበር ሥራዎች፣ በፈንጅ አወጋገድ ተግባራት፣ በሠው ኃይል ሥልጠና እና ሌሎች ወታደራዊ መስኮች ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የቀጠናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ዋነኛ ተዋናይ መሆኗን የጠቀሱት ጄነራል ፒየር ሺል፤ ለቀጠናው ደኅንነት የኢትዮጵያ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ብዙ የሚደነቅ ገጽታ እንዳለው በመግለጽ፤ ትምህርት የሚወሰድበት ሠራዊት መሆኑን መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።