የቀድሞው ብቃቱ የከዳው የፈርኦኖቹ ንጉስ ሞሃመድ ሳላህ…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሊቨርፑል ከሶስት አስርት አመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን ታላቅ አስተዋጽኦ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት የቀድሞ አቋሙ የከዳው የሚመስለው የፈረኦኖቹ ንጉስ ሞሃመድ ሳላህ፡፡
ሳላህ የተወለደው በፈረንጆቹ 1992 በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2012 ለስዊዘርላንዱ ባዜል በመፈረም ነበር የአውሮፓን እግር ኳስ የተቀላቀለው፡፡
በባዜል ቆይታው ሁለት የስዊዝ ሱፐር ሊግ ዋንጫን ያሸነፈው ሞሃመድ ሳላህ በ2014 ለምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በ11 ሚሊየን ፓውንድ ፊርማውን አኖረ፡፡
በቼልሲ ቤት በቂ የመጫወቻ ጊዜ ያላገኘው ሳላህ በጣሊያን ክለቦች ፊዮረንቲና እና ሮማ በውሰት ሲጫወት የቆየ ሲሆን ሮማ በ2016 በ15 ሚሊየን ዩሮ ቋሚ አደርጎ አስፈረመው፡፡
ሞሃመድ ሳለህ በሮማ እጅግ አስደናቂ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በሴሪአው ሮማን የዋንጫው ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
በ2017 በወቅቱ የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ 36 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ወደ እንግሊዝ በመመለስ ለመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ዝውውሩን ያደረገው ሞ ሳላህ በመጀመሪያው አመት የአንፊልድ ቆይታው በሁሉም ውድድሮች 32 ግቦችን በማስቆጠር ግሩም ጊዜን ማሳለፍ ችሎ ነበር፡፡
በጀርመናዊው አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ስር ከሳዲዮ ማኔ እና ሮቤርቶ ፌርሚኒሆ ጋር አስፈሪ የፊት መስመር ጥምረት በመፍጠር ከቡድን አጋሮቹ ጋር የመርሲሳይዱ ክለብ ትንሳኤ ምልክትም መሆን ችለዋል፡፡
ሊቨርፑል ከሶስት አስርት አመታት በኋለ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ግንባር ቀደም ሚና የነበረው ግብጻዊው ኮከብ ክለቡ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን በማሳካት ዳግም ወደ ሃያልነቱ እንዲመለስም አስችሏል፡፡
በ2024/25 የውድድር አመት ከቀዮቹ ጋር ዳግም የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፥ ባሳየው ድንቅ ብቃት የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ማህበር የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ለሦስተኛ ጊዜ በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን የግሉ አደርጓል፡፡
ሞ ሳላህ በግል ሦስት ጊዜ የእግር ኳስ ጸሃፊያን ማህበር የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን፣ አራት ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ የወርቅ ጫማ፣ ሁለት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ተጫዋች እንዲሁም ሁለት ጊዜ የሊጉ የአመቱ ጨዋታ አቀጣጣይ ሽልማትን አሸንፏል፡፡
በተጨማሪም በ2018 እና 2021 የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ደረጃን በሶስተኝነት እንዲሁም በ2025 የባሎንዶር ሽልማት አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀ ሲሆን የፑሽካሽ ሽልማትንም ያሸነፈ የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡
ከቀዮቹ ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን ማሳካት የቻለው ሞ ሳላህ ለሊቨርፑል ባደረጋቸው 300 ጨዋታዎች 188 ግቦችን በማስቆጠር የክለቡ ሶስተኛው የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡
በፈጣን ሩጫዎቹ፣ ተከላካዮችን በማለፍ ኳስ የመግፋት ክህሎቱና ግብ በማስቆጠር ብቃቱ እጅግ የሚወደሰው ሞ ሳላህ በዘንድሮ የውድድር አመት የቀደመው ብቃቱ ከድቶት የቡድኑ ዋነኛው ችግር መሆኑ በስፋት እየተነሳ ይገኛል፡፡
በ2025/26 የውድድር አመት በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ዘጠኝ ሽንፈት ያስተናገደው የአርኔ ስሎቱ ሊቨርፑል ባሳለፍነው እሁድ ወደ ለንደን አምርቶ ዌስትሃም ዩናይትድን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ሞ ሳላህ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡
ሳላህ በተጠባባቂ ወንበር ሲቀመጥ ከሚያዚያ ወር 2024 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሊቨርፑል በታሪኩ አስከፊ ጊዜን እያሳለፈ በሚገኝበት በዚህ የውድድር አመት ሳላህ በመከላከሉም ይሁን በማጥቃት ሂደት ቡድኑን እያገዘ ባለመሆኑ ተጠባባቂ ወንበር ላይ መሆን አለበት የሚሉ ድምጾች ተበራክተዋል፡፡
ሊቨርፑል ዛሬ ምሽት በሊጉ ከሰንደርላንድ ጋር በሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ የ33 አመቱ ግብጻዊ በጨዋታው በቋሚነት የመሰለፍና አለመሰለፉ ጉዳይ የሚጠበቅ ነው፡፡
በግብጽ የብሔራዊ ኩራት ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረው ሞ ሳላህ ለሀገሩ በ109 ጨዋታዎች 63 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፥ በ2019 በታይም መጽሄት በአለማችን ከ100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በአቤል ነዋይ