Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ስምምነቱ ዜጎችን ከሞት አደጋ የመለሰና የአዳጊዎች ተስፋ እንዲለመልም ያደረገ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ዜጎችን ከሞት አደጋ የመለሰና የአዳጊዎች ተስፋ እንዲለመልም ያደረገ ነው አሉ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈርሟል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፥ የሰላም ስምምነቱ ለክልሉ ሕዝብ የሰላም ጥያቄ ምላሽ የሰጠና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡

ለሰላም መቼም ቢሆን ረፍዶ አያውቅም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሰላም ስምምነቱ ዜጎችን ከሞት አደጋ ወደ ሕይወት የመለሰና አዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና ተስፋቸው እንዲለመልም ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በመነጋገር ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ በድጋሚ የታየበት ስምምነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ አጉል ጀብደኝነት ወደ ግጭት ይመራል፥ ጦርነት ውዱን የሰው ሕይወት ይቀጥፋል፥ በብዙ ጥረት የተገኘን ሀብትን ያወድማል፥ ብሎም ድህነትን፣ ድንቁርናንና ኋላ ቀርነትን ያስፋፋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ጥፋት ከሚያስከትሉ ተግባራት በመራቅ ለዘላቂ ሰላማችንና ለልማታችን በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ማናቸውም የፖለቲካ ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያለውን ጽኑ አቋም አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥ እንደ ዛሬው ስምምነት ተግባራዊ ርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም ነፍጥ አንሥተው በጫካ የሚገኙ የተወሰኑ ቀሪ ቡድኖች በኃይል የሚሳካ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ወደ ሰላም ሊመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዛሬውን የሰላም ስምምነት ለማዝለቅ፣ የግጭት ተግባራትን በጋራ በማውገዝ ለሰላም ዘብ መቆም ያሻል ያሉ ሲሆን፥ ይህ ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን በፌደራል መንግሥት ስም አመስግነዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለሕዝብ የሚያስብ ሁሉ ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.