Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጃዋርን ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የቅድመ ምርመራ ምስክር መሰማት ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2012 (ኤፍ. ቢ.ሲ) በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ተረኛ ችሎት አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የቅድመ ምርመራ ምስክር መሰማት ተጀምሯል።

ችሎቱ ባለፈው ቀጠሮ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለተጠርጣሪዎች እንዲደረግ ሰጥቶ የነበረው ትእዛዝ መፈጸሙን ተመልክቷል።

በሙሉ ምርመራ እንደተደረገላቸው የሚገልጽ ማስረጃ የፌዴራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጽሁፍ አቅርቧል።

በፍርድ ቤቱ ለተጠርጣሪዎች መመርመር አለመመርመራቸውን ላቀረበላቸው ማረጋጋጫ ጥያቄም መመርመራቸውን አረጋግጠዋል።
ችሎቱ ምስክሮችን መስማት ከመጀመሩ በፊት የፌደራል ፖሊስ አቶ ጃዋር መሀመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ ቦረና (ሃምዛ አዳነ) እና ሸምሰዲን ጣሃ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ የህክምና ማስረጃ ያቀረበ ሲሆን፥ ችሎቱም ይህን ይፋ አድርጓል።
አቶ ጃዋር ከደህንነታቸው አንፃር ባላቸው ሁኔታ ከግል ሐኪማቸው ጋር ሊገናኙ አለመቻላቸውን አቤቱታ አቅርበዋል።

ከሕክምና ጋር በተገናኘ አቶ ጃዋር ከግል ሐኪማቸው በስተቀር በመንግሥት ሆስፒታል እንዲታከሙ ቢጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ፖሊስ አስረድቷል።

ዐቃቤ ሕግም በዚህ ላይ ምላሽ የሰጠ ሲሆን÷ ሕመማቸው አጣዳፊ ከሆነ በግል ሐኪማቸው እንዲታዩ ቢባልም የግል ሐኪማቸውን ስልክ አላውቅም የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አብራርቷል።

አለም አቀፍ መርህ ለታሳሪ ህክምና ማሟላት ያስፈልጋል ያለው አቃቤ ህግ በግል ሃኪሜ ብቻ ማለታቸው አግባብ የለውም ብሏል።

የፌደራል ፖሊስም በፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል መታከም እንደሚችሉ ጠቅሷል።

ከዚህ በፊት አቶ በቀለ ገርባ ከሁለት ጊዜ በላይ በሆስፒታሉ ታይተዋል፤ ጤንነታቸው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲል ፖሊስ ምላሽ ሰጥቷል ።

ለአቶ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ ክፍል ካሜራ በመኖሩ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን በመጥቀስ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ምላሽ የሰጠው ፖሊስ ካሜራው የተቀመጠው ግቢው አዲስ በመሆኑ እና በተለይም በቤተመጽሃፍት ክፍል ውድ የሆኑ መጻሕፍት በመገኘታቸው መሆኑን ጠቅሶ ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት ክፍል መመቻቸቱን ገልጿል።

ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 መሠረት ተጠርጣሪዎች መብታቸው እና ጤናቸው መጠበቅ እንዳለበት ብሎም ከግል ሀኪሞቻቸው ጋር እንዲገናኙ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ከዚህ ባሻገር ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ሚሥጢራቸውን መጠበቅ በሚያስችል መልኩ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ያድርግ ብሏል።

ይህ ትእዛዙ የማይፈጸም ከሆነ በቀጣዩ ቀጠሮ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
አቃቤ ህግ ባቀረበው አቤቱታ ማለትም በዛሬው የምስክሮቼ ጭብጥ በፍርድ ቤት ማህተም ወጥቶ በማህበራዊ ሚዲያ መለቀቁን ደርሼበታለው፤ በዚህ ላይ እርምጃ አንዲወሰድ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ብሏል።

ፍርድ ቤቱ አቤቱታው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠትና የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ለነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.