የ15ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ15ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት 7 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ቀን 9 ሰዓት 30 ላይ የሊጉ መሪ አርሰናል ወደ ቪላ ፓርክ በማቅናት ከአስቶንቪላ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመሩት መድፈኞቹ በሊጉ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፈው በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ባለሜዳው አስቶንቪላ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን በአራቱ ጨዋታ ደግሞ በተከታታይ ድል አድርጓል፡፡
አርሰናል በ33 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የተቀመጠ ሲሆን ተጋጣሚው አስቶንቪላ በ27 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት የመጨረሻ ጨዋታዎች አርሰናል በሁለቱ ሲያሸንፍ አስቶንቪላም በተመሳሳይ በሁለት ጨዋታ ድል አድርጎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የሊጉ ጨዋታ ሲቀጥል ምሽት 12 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ሰንደርላንድን ያስተናግዳል፡፡
በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በሊጉ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
በውድድር ዓመቱ ለሊጉ ትላልቅ ቡድኖች ፈታኝ ሆኖ የቀረበው ሰንደርላንድ በበኩሉ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፉክክር ይጠበቃል፡፡
ሰንደርላንድ በዚህ የውድድር ዘመን ቼልሲን ያሸነፈ ሲሆን ከአርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር አቻ ተለያይቶ በማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ተሸንፏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
ቼልሲ በተመሳሳይ ሰዓት ወደ ቪታሊቲ በማቅናት ከቦርንማውዝ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ያለፉትን ሁለት ተከታታይ የሊጉን ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ቼልሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
ባለሜዳው ቦርንማውዝ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።
ኒውካስል ዩናይትድ ከበርንሌይ፣ ቶትንሃም ሆትስፐር ከብሬንትፎርድ፣ ኤቨርተን ከኖቲንግሃም ፎረስት ሌሎች በተመሳሳይ 12 ሰዓት የሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በኢንላንድ ሮድ ስታዲየም ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይገናኛል፡፡
በውድድር ዓመቱ ደካማ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኘው ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ጨዋታ ሲሆን ሊድስ ዩናይትድ ደግሞ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን በሊጉ ለማሳካት ይፋለማል፡፡
ባለፉት ተከታታይ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ወደ ተቀያሪ ወንበር የወረደው ሞሃመድ ሳላህ በዛሬው ጨዋታ ለሦስተኛ ጊዜ ተቀያሪ ወንበር ላይ ይቀመጥ ይሆን የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡
የሊጉ ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው ሲደረጉ 11 ሰዓት ላይ ብራይተን ከዌስትሃም እንዲሁም ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ፉልሃም ከክሪስታል ፓላስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
የ15ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ዩናይትድን ከወልቭስ ያገናኛል፡፡
በውድድር ዓመቱ በሊጉ ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ወልቭስ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!