መድረኩ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተሻሻለ የሥራ ባህል መትጋት እንደሚገባ መግባባት የተፈጠረበት ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ ሲካሄድ የቆየው የአመራሮች ስልጠና መድረክ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተሻሻለ የሥራ ባህል መትጋት እንደሚገባ መግባባት የተፈጠረበት ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
“በመደመር መንግስት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው 3ኛ ዙር የወረዳ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሥልጠና መድረኩን መጠናቀቅ በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሥልጠና መድረኩ የቀረቡ የስልጠና ሰነዶችና በመስክ ምልከታዎች አመራሮቹ ተጨማሪ አቅም የገነቡበትና እርስ በእርስ ልምድ የተለዋወጡበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
አመራሩ በስልጠናው ቆይታ ያገኘውን ግንዛቤ በተጨባጭ ወደ መሬት በማውረድ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል መቀየር እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡
ያለምነው ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን በተሻሻለ የስራ ባህል ለሕዝባችን የምንሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊነት ማረጋገጥና ማላቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በከተማችን ነዋሪዎች ያለውን አዳጊ የልማት ፍላጎትና ለዘመናት የተከማቸ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታት ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በማያቋርጥ ራስን የማብቃት፣ የፈጠራና የፍጥነት ዑደት ውስጥ ማለፍ እንደሚገባ መግባባት የተፈጠረበት የሥልጠና መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በትኩረት መስክነት በለየናቸው ሀገራዊ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ የቱሪዝምና ከተማ ልማት ዘርፎች እመርታን ለማስመዝገብ አመራሩ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና እንዲወጣ የጋራ መግባባት የፈጠርንበት ስኬታማ መድረክ ነበር ብለዋል።
በማያቋርጥ መፍጠር እና መፍጠን መርህ እየሠራን የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን ሲሉም ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡