ለኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኘው ተቋም…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ሞዴል በመጠቀም በምርምር፣ የሰው ኃይል በማብቃትና በቴክኖሎጂ ልማት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተወጣሁ ነው አለ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት፡፡
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀዳለ ተክሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ተቋሙ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማሳደግ ረገድ እስካሁን ከ150 በላይ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡
የተግባር ክህሎት ያላቸውን ቴክኒሻኖችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን በማብቃት ረገድ የኢንዱስትሪ ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ሞዴል በመጠቀምና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባባር የተግባር ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡
በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር በማከናወን ተኪ ቴክኖሎጂዎችን በማምረትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እያገዘ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ይዘት ከኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰው ኃይል ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የኢንዱስትሪ ተቋማትን ያሳተፈ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ማሻሻያ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡
ተቋሙ ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ተኪ ቴክኖሎጂዎችን ለማምረትና ለማባዛት የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር የራሱን ኢንተርፕራይዝ (ቴክኖቢዚያ) በማቋቋም የተግባር ስልጠናውን ከመደገፍ ባሻገር ተኪ ምርቶችን እያመረተ ለተጠቃሚ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬተሯ አክለውም ኢንስቲትዩቱ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተማሪዎችን በማብቃት ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የተማሪዎቹን የስራ እድል ለማሳደግ በስራ ላይ ልምምድና በኢንዱስትሪ ጉብኝት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ክህሎት እንዲያዳብሩ በማስቻል ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ