የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የክልሉ ሕዝብ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ ነው – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በዓሉ ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው እንዲመክሩ እና እንዲደምቁ እድል ፈጥሯል።
እንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች መክረው የመፍትሔዎች አካል እንዲሆኑ ለማስቻል፣ የጋራ ትርክትን በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር እና የሀገረ መንግሥትን ቅቡልነት ከፍ ለማድረግ ለተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት የራሱ አስተዋጽዖ ያበረክታል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዓሉ ባሕላዊ ትውፊቶችን እና ልምዶችን የሚለዋወጡበት ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ለወንድማማችነት እሴቶች ማበብ እና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለፌደራሊዝም ስርዓት መጠናከር እና ለጋራ ትርክት ግንባታ የራሱን አስተዋጽዖ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል በሀሳብ ልዕልና በመመራት ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የመመካከር እና የመወያየት ባሕልን በማላቅ የዳበረ የዴሞክራሲ እና የአካታችነት እሴቶችን ለማስረጽ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ እንደሆነም አመልክተዋል።
የዘንድሮውን በዓል የዘመናት ቁጭት መቋጫ፣ የአዲስ ንጋት ማብሰሪያ እና የማንሰራራት ዘመን ምልክት እና አሻራ የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ እና ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ በጋራ እሴቶች የተሳሰረች፣ በብዝሐነት ያጌጠች፣ በጋራ ትርክት የጸናች፣ በጋራ ሕልም ተስፋዋን ከፍ ለማድረግ የምትተጋ ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባቱ ረገድ ከወትሮው በላቀ በታታሪነት እና በትብብር መንፈስ ለመትጋት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ስርዓት የተደነገጉ የራስ አስተዳደር እና የጋራ አስተዳደር ማዕቀፎችን መሰረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ማንነት፣ ኢትዮጵያዊነት እና አንድነት ሚዛናቸውን ጠብቀው የሚራመዱበት ጠንካራ ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ሂደት ላይ ክልሉ የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በጋራ ጥረት ዕውን በማድረግ ሉዓላዊነቷ እና ብሔራዊ ክብሯ የተሟላ ሆኖ የብልጽግና ጉዞዋ እንዲሳካ ክልሉ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና አዳጊ የሕዝብ ጥቅሞችን ለማስከበር እና አዳጊ የሕዝቦች ፍላጎቶችን ለማሟላት መሰረታዊ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በሚደረገው እንቅስቃሴ የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!