የኢነርጂ መሠረተ ልማት ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ነው – ኮሚሽነር ሌራቶ ማታ
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢነርጂ መሠረተ ልማት ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ነው አሉ የአፍሪካ ኢነርጂና መሰረተ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌራቶ ማታ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ኢነርጂ ኢፊሸንሲ ጉባኤ በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ሌራቶ ማታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ÷ የአፍሪካ አህጉር ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት በሆነው የኢነርጂ አጠቃቀም ላይ በጋራ መስራት ይገባል።
የአህጉሪቱን የኃይል እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ኢነርጂ አጠቃቀም ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው÷ ያለውን የኃይል አጠቃቀም ማሻሻልና የኃይል እጥረትን ለመፍታት በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካ ለዘላቂ ልማት ወሳኝ በሆነው ኢነርጂ ላይ ያላትን እምቅ የኢነርጂ አቅም በአግባቡ ልትጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የአፍሪካ ኢነርጂ ልማት በጋራ ትሰራለች ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት በመፍጠር ለበርካታ ሀገራት ምሳሌ መሆኗን ጠቁመው÷ በዚህም ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታዘጋጅ መመረጥ መቻሏን አውስተዋል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ