Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካውያን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው – አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካውያን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)።

በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 17ኛ የአፍሪካ የመከላከያ መሪዎች ጉባዔ ተጠናቅቋል።

ጉባኤው አሕጉሪቱ እየተጋፈጠች ያለችውን የሽብርተኝነት፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎች የደኅንነት ቀውሶችን በተባበረ ክንድ መፍታት ላይ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

መሪዎቹ የአፍሪካን የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን የሌላ አሕጉር ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ እንዴት በራስ አቅም ብቻ መፍታት እንደሚቻል አጽንዖት ሰጥተው ተወያይተዋል።

ጉባዔው ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ በሶማሊያ አልሸባብን የመዋጋት ተግባራት፣ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በየሀገራቱ ያለው የውስጥ ግጭት፣ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የፋይናንስ ድጋፍ በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል።

አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባዔ ለሰላም ካላት ጠንካራ አቋምና እንደ አፍሪካዊ ተምሳሌትነቷ ተመርጣ ለተከታታይ ዓመታት እያስተናገደች መሆኗን አንስተው÷ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት ኢትዮጵያ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

ጉባዔው የአሕጉሪቱን ችግሮች በፍጥነት የሚፈታ የተባበረ የአፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አስፈላጊነት ላይ መወያየቱን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለአሕጉሪቱ ያላት አስተዋፅኦ የተንፀባረቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ከሀገራት ጋር መደረጉን ጠቅሰው÷ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ ሕዝብ ሠላም ላበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እውቅና መሰጠቱንም አመላክተዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የዓለም አቀፍና የጎረቤት ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ÷ በቀጣይ የአህጉሪቱን ችግሮች በትብብር እየፈቱ ለመሄድ ከስምምነት መደረሱን አመላክተዋል።

በየዓመቱ የሚካሄደውን ጉባዔ ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ስታስተናግድ የቆየች ሲሆን÷ ዘንድሮ ከሕዳር 29 እስከ ታሕሣሥ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መካሄዱን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook WMCC
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.