ለእናቶችና ሕጻናት ጤና ሥርዓት መሻሻል የሚውል 167 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእናቶችና ሕጻናትን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል ከአጋር ድርጅቶች 167 ሚሊየን ዶላር ተሰብስቧል አሉ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ።
የእናቶችና ሕጻናት ጤናን ለመደገፍ ኮምፓካት አግሪመንት የተሰኙ አጋር ድርጅቶችና መንግሥት በጋራ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ዶ/ር ደረጄ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሃብት ማሰባሰቡ ዋነኛ ዓላማ የእናቶችና ሕጻናትን የጤና ሥርዓት ጥራቱን ለማጠናከር እና ግብዓት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ ለማስቻል ነው፡፡
በዚህም ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት ጥቅም ላይ የሚውል ከአጋር ድርጅቶች 167 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ደግሞ ከዚህ ጋር የሚጣመር ተመሳሳይ ሃብት በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡
ለዘርፉ እድገት ተጨማሪ ሃብት የማሰባሰብ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው÷ በየዓመቱ 140 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ይህም የእናቶችና ሕጻናትን ጤና ለማስጠበቅ እንዲሁም በ2030 የእናቶችና ሕጻናትን ሞት በሚፈለገው ደረጃ ለመቀነስ በእጅጉ እንደሚያግዝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሃብቱ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት፣ ጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት እንዲኖረው ያስችላል፡፡
ድጋፉን እየሰጡ የሚገኙት የኮምፓክት ስምምነት 11 ረጅና አጋር ድርጅቶች መሆናቸው በመርሐ ግብሩ ተመላክቷል፡፡
በመሳፍን እያዩ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook WMCC
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!