Fana: At a Speed of Life!

ከአካውንቲንግ ባለሙያ ወደ ተዋጣለት ተዋናይነት…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በሚታዩት ከትዳር በላይ፣ ንጉሥ አርማህ፣ እምዬ ብረቷ እና ደጋግ ሰይጣኖች ላይ ይተውናል ተዋናይ የማታወርቅ ታደሰ።

በተለይም ብሔራዊ ቴአትር ሲታይ ቆይቶ ወደ ዓለም ሲኒማ በተዘዋወረው ከትዳር በላይ ተውኔት ላይ የትወና ብቃቱን አሳይቷል፡፡

ተዋናዩ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረገው ቆይታ÷ የ70 ዓመት እድሜ ባለፀጋ በሆነው ታሪካዊው ብሔራዊ ቴአትር ቤት መገኘት መታደል ነው ይላል።

እዚህ መድረክ ለመገኘት ተምሮ ይሰራበት የነበረውን የአካውንቲንግ ስራ ለቆ ከትውልድ አካባቢው ሻሸመኔ ጥበብን ፍለጋ አዲስ አበባ ከትሟል።

ህልሙን ፍለጋ ወጥቶ ተሳክቶለታልና ህልሜን እየኖርኩ ነው የሚለው ተዋናይ የማታወርቅ÷ ከአያቱ እግር ስር ፊደል ቆጥሮ ጥበብ ተምሮ ማደጉ ለዛሬው ጉዞ ስንቅ እንደሆነውም ይናገራል።

በትምህርት ቤትና በክበባት የነበረው ተሳትፎ የጥበብ ጀማሮና ፍላጎቱን የቀና አድርጎለታል።

በ”የእግዜር ጣት”ና ሌሎች ተውኔቶች የተጀመረው ትወና እስከ ባሕርማዶ በተሻገሩ ቴአትሮች ላይም እንዲሣተፍ አስችሎታል።

“ደጋግ ሰይጣኖች” በተሰኘው ቴአትር ላይ ዋና ተዋናይ ሆኖ መተወን የነበረበት ሰው ስላልቻለ የማታወርቅ እሱን ተክቶ በአጭር ጊዜ በማጥናት ቴአትሩ ለዕይታ እንዲበቃ በማስቻሉ አጃኢብ አስብሏል፡፡

ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ያጠናቀቀው የማታወርቅ ታደሰ ሲትኮምና ተከታታይ ድራማ ላይም የትወና ብቃቱን አሳይቷል፡፡

በቅድስት ዘውዱ

ተዋናይ የማታወርቅ ታደሰ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረገውን ቆይታ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ይከታተሉ👇
https://www.youtube.com/watch?v=9DPlXHw3NI0

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.