Fana: At a Speed of Life!

የፋይዳ መታወቂያን ተደራሽነትና አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ተደራሽነትና አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፡፡

በፕሮግራሙ የሳይበር ደህንነት ዳይሬክተር ካሳዬ ታፈሰ (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የባዮሜትሪክ መረጃዎችን ያካተተው የፋይዳ መታወቂያ የሰዎችን ማንነት በሚገባ ለመለየት አስችሏል፡፡

ይህም ከዚህ በፊት በባንኮችና ሌሎች ተቋማት አገልግሎቶች ላይ መታወቂያን አስመስለው በመስራት ሲፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎችን የሚያስቀር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ፋይዳ በኦንላይንም ሆነ በአካል የሚሰጥን አገልግሎት በአስተማማኝ እና በተቀላጠፈ ሁኔታ ማግኘት እንደሚያስችል ነው የገለጹት፡፡

የፋይዳ መታወቂያን ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ አሁን ላይ የተመዝጋቢዎች ቁጥር 29 ሚሊየን በላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ 90 ሚሊየን ዜጎችን ለመመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ÷ የተለያዩ አገልግሎቶችን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡

ለአብነትም በቅርቡ የተጀመረውን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከባንክ ሥርዓት ጋር የማጣመሩ ሥራ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ደንበኞች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የባንክ ሒሳባቸውን ከፋይዳ መረጃ ጋር የማጣመር ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የፋይዳ መታወቂያን ልክ እንደ ፓስፖርት የግለሰብ መለያ ለማድረግ ከሀገራት ጋር ትስስር የመፍጠር ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ለጥቃት ያልተጋለጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.