የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በተለያዩ ክልሎች እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት በተለያዩ ክልሎች በዛሬው ዕለት መሰጠት ጀምሯል፡፡
በዘመቻ መልክ ቤት ለቤት የሚሰጠው ክትባቱ ከታሕሣሥ 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ ተመላክቷል፡፡
በዚህ መሰረትም በአማራ ክልል ከ10 ዓመት በታች የሆኑ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳሉት ÷ ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በጤና ተቋማትና እና በትምህርት ቤቶች ይሰጣል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነብዩ ቤዛ ÷ ክትባቱ ለላለፉት 20 ዓመታት ሲሰጥ ቢቆይም በጥራት ማነስና በተደራሽነት ውስንነት በሽታውን መግታት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በቅደም ተከተል 75 ሺህ እና 207 ሺህ ለሚሆኑ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ጀምሯል፡፡
የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ እና ኡስማን መሃመድ