ኢትዮጵያና ኮንጎ ሪፐብሊክ በወታደራዊ መስክ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ከኮንጎ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ቻርለስ ሪቻርድ ሞንጆ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሀገራቱ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብርና በቅንጅት መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡
አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያና ኮንጎ ሪፐብሊክ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሀገራቱ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ፣ በጦር መሳሪያ ጥገና፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ አቅም በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል እድል እንደሚፈጥር ነው ያስገነዘቡት፡፡
አሁን ያለንበት ዓለም በትብብር መስራትን ይጠይቃል ያሉት ሚኒስሯ÷ ድንበር ዘለልና ሽብርተኝነት የመሳሰሉ ቀጣናዊ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ቻርለስ ሪቻርድ ሞንጆ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ሰላምና ደህንነት የበለጠ ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን ለመተገበር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አጽንኦት መስጠታቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡፡
በመላኩ ገድፍ