ከንቲባ አዳነች አራት ባለ4 ወለል የማምረቻ ሕንጻዎችን በሴፍቲኔት ታቅፈው ለነበሩ ነዋሪዎች አስረከቡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አራት ባለ 4 ወለል የማምረቻ እና መሸጫ ሕንጻዎችን በሴፍቲኔት ታቅፈው ለነበሩ ነዋሪዎች አስረክበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በመዲናዋ እየተተገበሩ ካሉ የዜሮ ግብ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ተረጂነት እና ልመናን ዜሮ ማድረግ ነው።
በዚህም በአዲስ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ የካ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች አራት ባለ4 ወለል የማምረቻና መሸጫ ሕንጻዎችን በሴፍቲኔት ታቅፈው ሲሰሩ ለነበሩ ነዋሪዎች አስረክበናል ብለዋል።
የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች 976 አንቀሳቃሾች ሲሆኑ÷ በ292 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁና ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ሕይወት በመለወጥና ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ520 ሺህ በላይ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር መቻሉን አስረድተዋል።
ከንቲባዋ ተጠቃሚዎች የተፈጠረውን የሥራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር በአጭር ጊዜ ውጤታማ በመሆናችሁ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡