የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አብሮነትን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን መቅረጽ አለባቸው – ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር ዜጋ ለመፍጠርና የትርክት ጫናን ለመመከት መስራት አለባቸው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት።
በኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ የተዘጋጀ የጥበባትና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ ÷ ባዳና ባንዳ የጋራ ግባቸው ኢትዮጵያን ማዳከም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጠላት ኢላማዎች ዓባይ፣ የባሕር በር፣ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬያችን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነታችን ላይ ነው ብለዋል፡፡
በጂኦ ስትራቴጂያዊ ቁመናቸው ከታደሉ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችና ይህንን ጂኦፖለቲካዊ ቁመና ለመለወጥ በኢትዮጵያ ላይ የቴክኖሎጂ፣ አካላዊ እና የትርክት ጦርነት ተካሂዶባታል ነው ያሉት።
በእነዚህ ጦርነቶቾ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የባሕር በር እንድታጣ መደረጉን እንዲሁም አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ የደህንነት ተጋላጭነቷ እንዲሰፋና ብሔራዊ አቅሟን በማዳከም በውስጥ ጉዳይ ብቻ እንድትተራመስ ጠላቶቿ ተግተው መስራታቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን መቅረጽ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡ የጠላት ኢላማ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞችን በማድረግ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ፣ ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት በመፍጠር ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ብሔራዊ አሰባሳቢ ትርክት ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ትልቁ መሳሪያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያን ታላቅ እያደረጓት ከቀጠሉ ልጆቿ መካከል የወለደቻቸው ጠቢባን ናቸው ብለዋል።
መንግሥት ለኪነ ጥበብ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡
በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የልማት ሥራ አስደናቂ የኪነጥበብ ሥፍራዎች መገንባታቸውን ጠቁመው÷ ይህንን ላከናወኑ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የጥበባት ፖሊሲ ረቂቅ እንዲሁም ከያንያን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት የጥበባት ካውንስል ሰነድ መጠናቀቁንና በመድረኩ ውይይት እንደሚደረግባቸው አመልክተዋል።