Fana: At a Speed of Life!

ለዓይን ህክምና አገልግሎት መሻሻል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዓይን ህክምና አገልግሎት መሻሻል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል አለ ጤና ሚኒስቴር፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተገነባ የዓይን ባንክ ማዕከል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በዚህ ወቅት÷ ዓይናችን የሕይወታችን ብርሃን ነው፤ ለዚህም መንግሥት የጤና አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በሀገሪቱ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች የዓይን ብርሃን ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው÷ ከዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት የማየት አቅማቸው የተዳከመ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሆኖም በጅማ የዓይን ባንክ መከፈቱ የዓይን ብርሃናቸው እንዲመለስ ለሚጠባበቁ ሰዎች ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የዓይን ባንክ ከማስፋፋት ጎን ለጎን የመሰረተ ልማት አቅርቦትን የማጠናከር ተግባር እንደሚሰራ አንስተው÷ በተለይም ለዓይን ህክምና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ነፃነት ወርቅነህ (ፕ/ር) የጅማ የዓይን ባንክ በማዕከል ያለውን ጫና በመቀነስ ከጅማና አካባቢው የዓይን ብሌን ከለጋሾች ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ጠቁመው÷ ይህም አገልግሎቱን ለማስፋፋትና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ከሰው ኃይል በተጨማሪ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው የዓይን ብሌን ለጋሾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አገልግሎቱን ወደ ክልሎች ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሁለተኛው የጅማ የዓይን ባንክ በሙሉ አቅሙ የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ስራውን እንደሚጀምር አመላክተዋል።

በተስፋሁን ከበደ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.