መንግሥት ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተግባር ይመልሳል – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ የልማት ተግባራትን በማከናወን የህዝቡን ጥያቄዎች በተግባር ይመልሳል አሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ‘የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች’ በሚል መሪ ሀሳብ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት÷ የመደመር መንግሥት የህዝቡን ችግር ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ሆና ያስመዘገበቻቸው ሁሉን አቀፍ ስኬቶች ከጀመረችው የብልፅግና ጉዞ የሚያደናቅፋት ሀይል አለመኖሩን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ታላቂ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የገጠሙትን ችግሮች በመፍታት ለዘመናት የሕዝብ ቁጭት ምላሽ መስጠቱን አንስተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው÷ የለውጡ መንግሥት በሰራቸው ስራዎችን ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
መንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉንም ገልጸው፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር በርካታ የስራ ዕድልን መፍጠር የሚያስችሉ ኢንሼቲቮችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን÷ ለዘማት ያልተጠቀምንባቸውን ነዳጅ እና ሌሎች ከፍተኛ የማዕድን ሀብቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም ጀምረናል ብለዋል፡፡
መንግሥት በአረንጓዴ አሻራ፣ በከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፉ ስራዎችን ማሳካቱን ገልጸዋል።
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በተሰራው ስራ የሀገሪቱን እምቅ የቱሪዝም አቅም ማነቃቃት ተችሏል ነው ያሉት።
በሲሳይ ለገሰ